
ዛሬ ላይ ቴክኖሎጂ ባንኮች እርስ በርስ ከሚፎካከሩባቸው መለኪያዎች አንዱ እንደመሆኑ ባንኮቹም በዚህ ረገድ የተሻሉ ሆነው ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛል፡፡ የቴክኖሎጂ የመጨረሻ ግብ ደግሞ የፋይናንስ ግብይቶችን ለደንበኞች ቀላልና ምቹ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን፣ ባንኮችም በየጊዜው ያሏቸውን ደንበኞች ለማቆየትና አዳዲሶችንም ለመመልመል የሚረዷቸውን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በስራ ላይ ያውላሉ፡፡
ለአብነትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብዛኞቹ ባንኮች በስራ ላይ እያዋሉት የሚገኘው የደንበኞች የኦንላየን ምዝገባ (Digital On-boarding) ተጠቃሽ ነው፡፡ይህ ደንበኞች ቅርንጫፍ መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ስፍራ ሆነው በኦንላየን ሂሳብ የሚከፍቱበት ወይም ደግሞ አዳዲስ ኘሮዳክቶችን ለመጠቀም የሚመዘገቡበት አሰራር (Digital On-boarding) በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን ጥቂቶቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡
የደንበኞችን ምቾት የጠበቀ አገልግሎት (Customer Convenience): ይህ የኦንላየን የምዝገባ ሂደት ደንበኞች ወደ ቅርንጫፍ ሄደው ፣ ረጅም ሰልፍ ጠብቀውና የተለያዩ ፎርሞችን ሞልተው አካውንት የሚከፍቱበትንና የተለያዩ ኘሮዳክቶችን ለመጠቀም የሚመዘገቡበትን ረጅም ሂደት ያስቀራል፡፡ በአጭሩ በፊት ብዙ ሰዓት የሚወስደውን የምዝገባ ሂደት አሁን በደቂቃዎች ውስጥ ባሉበት ሆነው በስልካቸው ወይም በላኘቶኘ ኮምፒውተራቸው ማከናወን ይችላሉ፡፡
የመረጃ ስህተትን ይቀንሳል (Minimize Data Error): በኦንላየን ምዝገባ ስርዓት ወቅት መረጃን የማጣራት ሂደት (Validation) ስለሚኖር እንዲሁም በእጅ (Manually) የሚገባ ባለመሆኑ ፣ ሰራተኞች በሚያስገቧቸው የተለያዩ መረጃዎች ላይ ለምሳሌ ቁጥር፣ ስም፣ አድራሻ … ወዘተ ላይ የሚፈጠርን ስህተት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፡፡
የበለጠ ተደራሽነት (Financial Inclusion): ብዙ ጊዜ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ወደ ባንክ መጥተው ሂሳብ የመክፈት ፍላጐት የላቸውም፡፡ ለምን እንደሆነም ሲጠየቁም በባንኮች ላይ ዕምነት ያለመኖር ፣ በቅርባቸው ቅርንጫፍ አለማግኘት፣ ለምዝገባ የሚረዱ ማስረጃዎች ያለመኖር … ወዘተ የሚሉ ምክንያቶችን ይደረድራሉ፡፡ ታዲያ የኦንላየን (Online) ምዝገባ እነዚህን ሁሉ የደንበኞች ስጋቶች የሚቀርፍ ነው፡፡
የመረጃ ደህንነት (Data Security): በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚከሰቱ የማጭበርበር ወንጀሎች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙት እንደ መታወቂያ ባሉ ማንነትን የሚገልጹ የተሳሳቱ ሰነዶች ነው፡፡ ታዲያ በዚህ የኦንላየን የምዝገባ ሂደት የተለያዩ የደንበኛን ማንነት የሚገልጹ መረጃዎችን የማጣራት መንገዶች (Biometric Means) የተሻሉ በመሆናቸው፣ እንዲህ አይነቶቹን ወንጀሎች በመቀነስ ረገድ በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡
ወጪ ቆጣቢነት (Cost Optimization): የኦንላየን ምዝገባ አንድ ቅርንጫፍ ደንበኛን በአካል ለመመዝገብ የሚያወጣውን የወረቀትና የተለያዩ ተያያዥ ወጪዎችን ያስቀራል፡፡
የሰራተኞችን የስራ ሰዓት ይቆጥባል (Save Employees’ Time): በዚህ የኦንላየን ምዝገባ ሠራተኞች ዕለት ተዕለት ከደንበኞች ጋር ከሚያደርጉት ግንኙነትና አልፎ ተርፎም አላስፈላጊ ንትርክ ወጥተው የተሻለ ስራ በትኩረት እንዲያከናውኑ ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡
ወጥነት ያለው አገልግሎት (Uniform Service): ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋል እንደ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ፍላጎት የሚስተናገዱት ደንበኞች ተመሳሳይና ወጥነት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡
በአጭሩ ዛሬ ላይ ፈጣን የሆነ የኦንላየን ምዝገባ በባንኮች መካከል አንዱ የመወዳደሪያ መስፈርት እየሆነ መጥቷል፡፡ ባንኮች ደንበኞቻቸው ጋር ተደራሽ ለመሆን ርቀት አሊያም የተፈጥሮ አቀማመጥ አይገድባቸውም፡፡ በመሆኑም አሁን አሁን ቅርንጫፎችን እንደ ድሮው በየአካባቢው የመክፈቱ ነገር በእጅጉ ቀንሷል፡፡
ባንካችን አቢሲንያም እጅግ ዘመናዊ የሆነውን ደንበኞች ባሉበት ስፍራ ሆነው በኦንላየን ሂሳብ የሚከፍቱበትንና የተለያየ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበትን የአፖሎ ዲጂታል ባንክ በስራ ላይ ካዋለ በርካታ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡ አፖሎ የተለያዩ የፋይናንስ ተደራሽነት መሰናክሎችን በማስወገድ ርቀት ሳይገድበው ተደራሽ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሉበት ስፍራ ሆነው አነስተኛ የብድር ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡
አፖሎ በተለይም በአቅራቢያቸው የባንክ ቅርንጫፍ የሌለ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደ አነስተኛ ብድር (Micro Loans) ፣ የቁጠባና እንዲሁም በአነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ ያልተገደበ ገንዘብ የማስተላለፍ እና የመቀበል አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ሌሎች እንደ አየር መንገድ ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የት/ቤት ክፍያ፣ የዲ.ኤስ.ቲቪ እና ሌሎችም የአገልግሎት ክፍያዎችንም በቀላሉ ማከናወን ያስችላል፡፡
በመሆኑም በሃገራችን በየትኛውም ክፍል የሚገኝ ደንበኛ የሞባይል ስልኩን በመጠቀም ለሚፈልገው ዓላማ አነስተኛ ብድር መውሰድና ሌሎች ከላይ የተዘረዘሩትን የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላል፡፡ አፖሎ ዲጂታል ባንክ ይህን በማድረግ የግለሰቦችን የፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ከማሟላትም ባሻገር አካታች የፋይናንስ ስርዓት እንዲስፋፋ በማድረግ ለሃገር ኢኮኖሚ ዕድገትም የበኩሉን አስተዋጾ ያደርጋል፡፡
ትልቅ ርዕይ ሰንቆ የተነሳው አፖሎ ዛሬ ትግበራ ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየታየበት ነው፡፡ ይህም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ባለው የፈጣን ብድር ተጠቃሚዎች፣ በአስቀማጮችና እንዲሁም የግብይት ብዛት የሚገለጽ ነው፡፡
በዚህ መሰረት እ.ኤ.አ እስከ 2025 መጨረሻ ድረስ የአፖሎ ዲጂታል ባንክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይህ ከፍተኛ የተጠቃሚዎች መሰረት ባንኩ የደንበኞችን ምቾት የጠበቁና ጥሩ ድጋፍም የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ በማዋል አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብና ለመቆየት የሚያደርገውን ጥረትና አቅም ማሳያ ነው፡፡
ሌላው የአፖሎ ዲጂታል ባንክ አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ 124 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ወደ 9 ሚሊዮን የሚጠጋ ግብይት ወይም ክፍያ የተካሄደ ሲሆን ይህም የሚያሳየው የአፖሎ ኘላትፎርም አገልግሎቱን ቶሎ ቶሎ የሚጠቀሙ (Active users)ደንበኞች እንዳሉት ማሳያ ነው፡፡
በሌላ በኩል ዛሬ ላይ ደንበኞች በአፖሎ በ9 ከመቶ ወለድ ከ 1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ አድርገዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ደንበኞች ምን ያክል በአፖሎ ዲጂታል ባንክ ላይ ዕምነት እንዳላቸውና መተግበሪያውንም በሚገባ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ያመለክታል፡፡
የአፖሎ ልዩ መለያ የሆነውን ፈጣን ብድርን በተመለከተ፣ የተበዳሪዎች ቁጥር በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ የጨመረ ሲሆን እስካሁን የተሰራጨው ብድር በአጠቃላይ ከ 3 ቢሊዮን ተሻግሯል፡፡ አፖሎ በዛሬው በፍጥነት በሚለዋወጥ ከባቢ ውስጥ ለደንበኞቹ ባሰቡት ሰዓት አስቸኳይ ብድር በማመቻቸት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ይሄ ማሳያ ነው፡፡
ታዲያ በአፖሎ ዲጂታል ባንክ ከሚለቀቁ ብድሮች ጋር ተያይዞ ስጋትን (Risk) ለማስቀረትና ተቆጣጣሪው አካል ያወጣቸውንም መለኪያዎች ለማሟላት ሲባል የብድር አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ክትትል ይደረጋል፡፡ ይህም አስቀድሞ የሚከናወን የስጋት አስተዳደር (Risk Management) የማይመለሱ ብድሮችን ከማስቀረትም በላይ ባንኩ የፋይናንስ ጤንነቱ አደጋ ላይ ሳይወድቅ፣ ይህን ጠቃሚ አገልግሎት ለደንበኞች ሳይቋረጥ እንዲሰጥ የሚረዳ ይሆናል፡፡
በመጨረሻም ምንም እንኳን አፖሎ ዲጂታል ባንክ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ቢሆንም፣ አገልግሎቱ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉ አንዳንድ ተግዳሮቶች ግን አልጠፉም፡፡ ለአብነት የደንበኞች የዲጂታል ዕውቀት (Digital Literacy)ውስን መሆን፣ በአንዳንድ ስፍራዎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ያለመኖር፣ የደንበኞች የስልክ ወይም የላኘቶኘ የጥራት ደረጃ … ወዘተ አዳዲስ ተመዝጋቢዎች ላይ ችግር እየፈጠረ ይገኝል፡፡ ታዲያ ይህንን ችግር ለመቅረፍና የደንበኞቹን ቁጥር ለማሳደግ፣ በአሁኑ ሰዓት የሚመለከታቸው የባንኩ የስራ ክፍሎች በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛል፡፡